መልክዐ ተክለሃማኖት - ክፍል ሶስት
፪. ሰላም ለዝክረ ስምከ በጥንተ ፊደሉ መስቀል ስም ክቡር ወስምልዑል። ተክለሃማኖት ማቴዎስ በዓለ ቀዳማይ ወንጌል ከመእወድሰከ መጠነ አውሥኦተ እክል። ማዕሠረ ልሳንየ ትፍታሕማርያም ድንግል።
ትርጉም
የስምሀ መነሻፊደል የመስቀልምልክት ለሆነውእና ክቡር ገናናለሆነው ስምአጠራርህ ሰላምእላለው ።የወንጌልተቀዳሚ ስምማቴዎስየተባልክተክለሃይማኖትሆይ እንደችሎታዬአመሰግንህ ዘንድአንደበቴ ትፈታልኝ ዘንድ ድንግል ማርያምን እማልዳለሁ።
የአባታችን የቅዱስ ተክለሃማኖት የስማቸው መነሻ ፊደል ’ተ’ የመስቀል ቅርጽ ያለው ነው የስማቸውም ትርጉም ተክለ አብተክለ ወልድ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው። ይህም በስማቸው ላይ ስመ እግዚአብሔር እንዳለ ያስረዳናል። በገድላቸው እንደተጻፈው ይህንን ስም አባታችን ያገኙት የመንፈሳዊ ተጋድⶀአችው የቅርብ ረዳት በሆነው በቅዱስ ሚካኤል አማካኝነት ነው ገድ ተክ፳፰ ፤፲፪ የቀድሞ ስማቸው ፍስሐ ጽዮን ነው ትርጉሙም የጽዮን ፤የቤተክርስትያን ፤የእመቤታችን ደስታ ማለት ነው ። በአጠቃላይየአባታችን የቅዱስ ተክለሃይማኖት ስም የእግዚአብሄርን ክብር የሚገልጽ ልዩ መንፈሳዊ መልክዕት የያዘ ስም ነው። ስለስማቸው ለመግቢያ ያህል ይህንን ካልን መጽሐፍ ቅዱስ ስለቅዱሳን ስም ምንእንደሚል አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት።
፩. በቅዱሳን ስም ላይ የእግዚአብሔር ስም ይከብራል
« በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት» ዘጸ፳፫፤፳፩
፪ .የቅዱሳን ስም ከስም ሁሉ የሚበልጥ ነው
«……..ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የሚበልጥ መታሰቢያ ስም ………» ኢሳ፶፮፤፭
፫.የቅዱሳን ስም ዘላለማዊ እና የማይጠፋ ነው
«የማይጠፋም ዘላለማዊ ስም እሰጣቸዋለሁ» ኢሳ፶፮፤፮
፬. በቅዱሳን ስም የእግዚአብሔር ቤት እና ቅጽሩ በመታሰቢያነት ይሰየማል
«በቤቴ እና በቅጽሬ ውስጥ……. የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ» ኢሳ፶፮፤፭
፭. በሰማያዊት ቤተ መቅደስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስምቀጥሎ የቅዱሳኑ ስም ተጽፎአል
«በእነርሱም የአስራ ሁለቱ የበጉ ሃዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር» ራእይ፳፩፤፲፬
፮. በቅዱሳን ስም ዝክር ማዘከር ፤ በጎ ሰራ መስራት ሰማያዊ ዋጋ አለው
«ከነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀመዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋባትም ።» ማቴ፲፤፵፪
እንግዲህ የቅዱሳኑ ስም ይህን ያህል የከበረ ከሆነ ለከበረው ስማቸው ሰላምታ መስጠት ምን ነውርነት አለው? ስማቸው የእግዚአብሔር ስም የሚገለጥበት ከሆነ ለስማቸው ክብር መስጠት የእግዚአብሔርን ስም ማክበር አይደለምን? ስማቸው በሰማያዊት ቤተ መቅደስ በክብር ከተጻፈ በስማቸው የእግዚአብሔር ቤት የሚሰየም ከሆነ ለስማቸው ክብር ሰላምታ መስጠት እንዴት ሊገርመን ይችላል? በስማቸው የሚሰራ በጎ ስራ ሰማያዊ ዋጋ ካለው የቅዱሳኑን ስም በማወደስ ጸጋና በረከት አይገኝምን? በአባታችን በቅዱስ ተክለሃይማኖት መልክዐ ጸሎታቸውም ላይ ለስማቸው ሰላምታ እና በጸጋ ምስጋና ቢቀርብላቸው መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት ያድረገ ነው ከላይ እንደተዘረዘርው እግዚአብሔር አምላክ የወዳጆቹን ክብር በስማቸው ቀርቶ በለበሱት ልብስ ፤ በረገጡት መሬት ፤በጥላቸውስ እንኳን ሳይቀር ይገልጽ የለምን? ቅዱስ ጳውሎስ በልብሱ እራፊ ጨርቅ ድውያንን ይፈውስ ነበር፤ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው ድውያንን ይፈውስ ነበር(የሐዋ፭፤፲፭ የሐዋ፲፱፤፲፪) ኦርቶዶክሳዊያን ምእመናን በቅዱሳኑ ስም እግዚአብሔር ድንቅ ስራዎችን እንደሚሰራ ያምናሉ በስማቸውም የቅዱሳንን አምላክ ይማጽናሉ ስለዚህም ነው የአባታንን ስም እያነሱ መጸለይ ተግቢ መሆኑን ከመልክዐ ጸለታቸው የተመለከትነው።
፫. ሰላም ለስእርተ ርእስከ በኅሊና አምላክ ዘተፈቅዳ ። እንተ ቦን ግልባቤ አምሳለ ሠላስ ደቂቀ ይሁዳ። ተክለ ሃይማኖት ማርቅስ ጸሐፌ መንክራት ውስተ ሰሌዳ ። አበውእ ለከ እግዚኦ ዘስብሐተ ጋዳ። ህየንተ ወርቅወብሩር ጸዐዳ።
ትርጉም
እንደ ይሁዳ ልጆች መጎናጸፍያ ለሆኑትና የቁጥራቸውብዛት በአምላክ ዘንድ ለሚታወቅ በራስህ ላይ ለሚገኝ የጸጉርህ ብዛት ሰላም እላለሁ ። እንደ ቅዱስ ማርቆስ ድንቅ የምትሆንወንጌልን የጻፍክና የሰበክ ተክለሐይማኖት ሆይ በወርቅ በብር ፈንታየምስጋና እጅ መንሻ አቀርብልሃለሁ።
ይህ ሰላምታ ከአባታችን ተክለሕዋሳት መካከል የጸጉራቸውን ክፍል የሚያወድስ ክፍል ነው ከንባቡ እንደምንረዳው የአባታችን የጸጉራቸው ብዛት በአምላክ ዘንድ እንደሚታወቅ ይገልጻል። ይህም እውነት ነው ጌታ በወንጌል ሲያስተምር እንኳንስ የአባታችንየእያንዳንዳችን የጸጉር ብዛት በእግዚአብሔር የተቆጠረ መሆኑን ገልጾልናል። «የእናንተ የራሳችሁ ጸጉር ሁሉ እንኳን የተቆጠረ ነው» ሉቃ፲፪፤፯
ስለዚህም በመልክዐ ጸሎታቸው ላይ የአባታችን የራሳቸው ጸጉር ብዛት በእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚታወቅ መገለጹ ትክክል ነው ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ልዑል እግዚአብሔር በመረጣቸው ቅዱሳን በጸጉራቸውም ሳይቀር ኃይሉን እንደሚገልጽ ስለ ጸጉራቸው በተለየ ሁኔታ የተነግረላቸውን መስፍኑ ሶምሶንን እና መጥምቁ ዮሐንስን ማንሳት ሃሳቡን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል። በሶምሶን ላይ የእግዚአብሔር ኃይል የተገለጸው በጸጉሩ ነበር። ለዚህም ነው ሶምሶን እራሱ እንዲህ በማለት የተነገረው «እኔ ከናቴ ማህጸን ጀምሬ ለእግዚአብሔር የተለየው ሰው ነኝበራሴ ላይ ምላጭ አልደረሰም የራሴንም ጸጉር ብላጭ ኃይሌ ከኔይሄዳል እደክማለሁም እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ» መሳፍ ፲፮፤፲፯። አዎ ቅዱሳንን እግዚአብሔር ከማህጸን ጀምሮ ይመርጣል በተለያዩ የህዋሳት ከፍሎቻቸውም ኃይሉን ይገልጻል አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በፈቃደ አምላክ በብስራተ መልአክ ከማህጸን የተመረጡ ጻድቅ ናቸው። ከራስ ጸጉራቸው አንስቶ መላ ህዋሳቶቻቸውን ለእግዚአብሄር የተለዩ ናቸው ስለዚህም በመላአካላቸው ሊወደሱ ሊመሰገኑ ይገባል።
ሌላው በዚህ ክፍል ላይ የተገለጸው አባታችን ልክ እንደ ቅዱስ ማርቆስ ግሩም ድንቅ የምትሆን ወንጌልን እንደጻፉና እንደሰበኩ ነው። በዕርግጥም አባታችን ቅዱስ ተክለሐይማኖትሐዲስ ሐዋርያ የወንጌል ሰባኪ ናቸው በሰው ልብ ላይ ወንጌልን ስለጻፉ የወንጌም ጸሐፊ ናቸው። ቅዱስ ተክለሃይማኖት ወንጌልን አልሰበኩም የሚል ተከራካሪ ቢነሳ ግን ገድላቸውን አንብበህ ፍረድ ከማለት ውጭ ምንም ሊባል አይቻልም። በምድረ ኢትዮጵያን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ተዘዋውረው ብዙዎችን ከአምልኮተጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ የመለሱ ቅዱስ ተክለሃይማኖት አይድሉምን? ከዚህ በላይ ወንጌልን መስበክ አለን? ቅዱስ ማርቆስ ከግብጽ ጣኦታት ጋራ ብዙ መከራ እየተቀበለ ተጋድሎ ወንጌልን እንደሰበከ አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በአገራችን የተለያዩ ስፍራዎች በመዟዟር ብዙ መከራ እየተቀበሉ አምልኮተ ጣኦትን እያጠፉ ወንጌልን ሰብከዋል ለዚህም ነው በወንጌላዊው በማርቆስ የተመሰሉት። የአባታችንን የቅዱስ ተክለሃይማኖትን ትሩፋትንና ገድልን አለመመስከር ለኢትዮጵያ ምድር ከቶ አይሆንላትም። በምድሪቱ ላይ የተከተቡ የታሪክ አሻራዎች በሙሉ አባ ተክለ ሃይማኖት አባተክለሃይማኖት እያሉ ይጮሃሉና።
አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን ያብዛልን
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር