መልክዐ ተክለ ሃይማኖት - ክፍል ሁለት
፩. ሰላም ለፅንሰትከ ወለልደት ከእምከርሥ። አመ ዕሥራ ውረቡዑ ለወርኃ ታኅሣሥ። ተክለሃይማኖት በኩሉ ወበውስተ ኰሉውዱስ። ናሁ ወጠንኩ ወዕቤ ለስብሓቲከ ሐዲስ። በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ።"
ትርጉም
ተክለሃይማኖት ሆይ አስቀድሞ በማህጸን ለተጸነስከው ጽንሰትህና በታህሳስ ሃያ ዐራት ቀን ለተወለድከው መወለድህም ሰላም እላለው በሁሉ ዘንድ የተመሰገንክ ተክለሃይማኖት ሆይ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብዬ አዲስ የሚሆን ምስጋናህን እጀምራለሁ።
በክፍል አንድ ጽሑፋችን ሰላም ለፅንሰትከወለልደትከ እምከርሥ። አመ ዕሥራ ውረቡዑ ለወርኃ ታኅሣሥ። የሚለውን የአባታችንን ፅንሰታቸውን እና ልደታቸውን የሚያወድሰውን ክፍል ተመልክተን ነበር በዚህ ጽሁፋችን ደግሞ ተክለሃይማኖት በኩሉወበውስተ ኰሉውዱስ ። ናሁ ወጠንኩ ወዕቤ ለስብሓቲከ ሐዲስ። በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ። ትርጉም ፤ በሁሉ ዘንድየተመሰገንክ ተክለሃይማኖት ሆይ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ ብዬ አዲስ የሚሆን ምስጋናህን እጀምራለሁ።
በቅድስት ቤተክርስትያን ስርአት መሰረት የማንኛውም ተግባር መጀመርያ ስመ ስላሴን መጥራት ነው የምታድርጉትን ሁሉበጌታ ስም አድርጉት ስለተባለ የጸሎትም መጀመርያ በስላሴ ስም ማማተብ ነው ምእምናን ጸጋ የሚያግኙበት የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበት ምስጢረ ጥምቀተት እንኳን የሚፈጸመው በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው ማቴ ፳፰፤፲፱ ለዚህም ነውየአባታችን ምልክዐ ጸሎታቸው ሲጀመር በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ የተባለው ። ይህም እያንዳንዱ ክርስትያን የግልምሆነ የማህበር ጸሎት ሲያደርግ በስላሴ ስም ማማተብ እንዲገባ ያስተምረናል ጌታም በወንጌል እንዲህ ብሎ ነግሮናል «ወደ አብ እሄዳለውና አብም ስለወልድ እንዲከበር በስሜየምትለምኑትን ሁሉ እኔ አደርገዋለሁ» ዮሐ ፲፬፡፲፫ በተጨማሪም «በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ እኔም ስለናንተአብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም»ዮሐ፲፮፡፪፮
በስሜ የምትለምኑትን ማለት በስመ ተወላዲ አምናችሁ ወልድን ተወላዲ ብላችሁ በስመ ወላዲ አምናችሁ አብንወላዲ ብላችሁ በስመ ሰራጺ አምናችሁ መንፈስ ቅዱስን ሰራጺ ብላችሁ የምትለምኑትን እኔ አደርገዋለው በማለት በስልጣን ከአባቱ ከአብ ከሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል መሆኑንም ጭምር አስግንዝቦአል ። እንግዲህ የቅዱስ አባታችን መልክዐ ጸሎታቸው በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ተብሎ መጀመሩ መጽሐፍ ቅዱስን ምሰረት ያደረገ መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ይሏል። በሁሉ ዘንድ የተመሰገንክ ቅዱሳን በሁሉ ዘንድ የከበሩ የተመሰገኑ እንደሆኑ የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ ያስተምረናል በሁሉ ዘንድ ማለት በሰዎች በመላዕከትእና በእግዚአብሔር ዘንድ ማለት ነው ። እግዚአብሔር አምላካችን ለቅዱሳኑ ከሚሰጣቸው ጸጋ አንዱ በሁሉዘንድ መወደድ ፤ መፈራት፤ ግርማ ሞገስ እና በጸጋ መመስገን ነው ይህንንም ለመረዳት የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችንመመልከት ይቻላል።
የሚባርኩህንም እባርካለው ዘፍ12፡3 ርዕሰ አበው ለሆነው ለአባታችን ለአብርሃም በተነገረው በዚህ ኃይለ ቃል እንደምንመለከተው ቅዱሳንን የሚባርክ የሚያመሰግን እርሱ እንደሚባረክ በረከተ ስጋ ወነፍስ እነደሚያገኝ ቅዱስ ቃሉ በግልጽ ያስቀምጣል ። ስለዚህም ከቅዱሳን አንዱ የሆኑትን አባታችንን ቅዱስተክለሃይማኖትን ማመስገን በረከተ ስጋ ወነፍስ የሚያሰጥ መጽሐፍቅዱሳዊ መሰረት ያለው እንጂ የስጋና የደም ትምህርት አይደለም። ዛሬ ማንም ተነስቶ የአባታችንን ቃል ኪዳን አማላጅነት ለማስተባበል ቢሞክር፤ የሚገባቸውንም የጸጋ ምስጋና ከማቅረብ ቸል ቢል ወይም የትዕቢት የጽርፈት ቃል ቢናገር ከሁሉ አስቀድሞ የሚጎዳው ራሱን ነው ምክንያቱም በቅዱስ ቃሉ እንዲህ ተብሎ ስለተጻፈ የሚረግሙህንም እረግማለው ዘፍ12፤3
በተጨማሪም ጻድቃንን የሚጠሉ ይጸጸታሉ መዝ33፤21 እንዲሁም ጌታ ራሱ በወንጌል እናንተንም የጣለ እኔንይጥላል ሉቃ10፤16 እንግዲህ በቅዱሳን ላይ የማይገባ የድፍረ ትንግግር መናገር የእርግማን ፤የውድቀት እና የዘላለማዊ ጸጸት ውጤት ከሆነ አንዳንዶች ስለምን ወደዚህ ድፍረት ገቡ? በእርግጥ ሐዋርያውቅዱስ ጴጥሮስ በመልዕክቱ ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ስልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም 2ጴጥ2፤11ብሎ እንደገለጸው ካደረባቸው መንፈሰ ጽርፈት ተነስተው የስድብ መሳርያ ቢሆኑ የሚደንቅ ነገር አይደለም። ለቅዱሳኑ ክብር የሚቆረቆር እግዚአብሔር ግን ዝም አይልም በቅዱሳኑ ላይ ስለምትሰነዘር እያንዳንዷ ቃል ይፈርዳል ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በኦሪት ዘኁልቁ ምዕራፍ ፲፪ የተዘገበው ታሪክ ነው ። የሙሴ ወንድም ካህኑ አሮንእና እህቱ ማርያም በታላቁ ነቢይ ሙሴ ላይ እንዲህ በማለት የድፍረት ቃል ተናግሩ «በእውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻተናግሮልን ? በኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን አሉ» ዝኁ፲፪፡፪ ይህንንም የሰማ እግዚአብሔር በጣም ተቆጣ ሶስቱንም ወደ ቤተመቅደሱ እንዲመጡ ከጠራቸው በኋላ በሚያስፈራ ግርማ በአምደ ደመና ወረደ ካህኑ አሮንንና እህቱ እንዲህ በማለት ተቆጣቸው «ቃሌን ስሙ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በህልም አናግረዋለሁ ባርያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለው በምሳሌ አይደለም የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል በባርያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድስ ለምን አልፈራችሁም አለ» ዘኁ ፲፪፡፮ ፰ ወዲያውኑ ማርያም እህተሙሴ በለምጽ ነደደች አሮንም ካህን ስለነበር ከህዝባዊያኑ ጋር ቅጣቱ ስላልተገለጸ እንጂ ተቀጥቶአል እግዚአብሔር አምላክም መልሳቸውን እንኳን ሳይጠብቅ ትቶአቸው ሄደ ። አዎን ዛሬም በቅዱሳኑ ላይ ማንኛውንም አይነት የድፍረት ንግግር የሚናገሩ ተጸጽተው ንስሃ ካልገቡ ቅጣቱ የማይቀር ነው። ለጊዜው በሕይወተስጋ ሳሉ በክህደት ለምጽ ሲነዱ ይኖራሉ በኋላም ዘላለማዊ እሳት እንደ ለምጽ ሲበላቸው ይኖራል። እንግዲህ ምን እንላለን ለቅዱሳኑ የሚገባውን ክብር ከመስጠት ወደኋላ ብለን እግዚአብሔርን እናስቆጣውን ? አይደለም ተገቢውን ክብር ለወዳጆቹ እናቅርብ እንጂ። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርጋ አባታችን ቅዱስ ተክለሃማኖትን በሁሉ ዘንድ የተመሰገንክ እያለች ታወድሳቸዋለች ። አዎን በእውነት አባታችንቅዱስ ተክለሃይማኖት በሁሉ ዘንድ የተመሰገኑ ናቸው ለዚህም ገድል ትሩፋት የፈጸሙባት ምድረ ኢትዮጵያ ቋሚ ምስክር ናት። የአባታችን የቅዱስ ተክለሃይማኖት ሥራ በኢትዮጵያ ብቻ ያበራ አይደለም ታሪካቸውን መርምረው የተደመሙበት አውሮፓዊያን ሳይቀሩ በቤተ መዛግብቶቻቸው ከትበው አስቀምጠውታል ።
በቃልኪዳናቸው የታመኑ ግብጻዊያን ክርስትያኖች እንኳን በስማችው ቤተክርስትያን አሳንጸው በረከታቸውን ይሳተፋሉ። በምድረ አሜሪካም ታላቅ የጸሎት ሰው ተብለው ሰዕላቸው በቤተመዛግብቶቻቸው ሳይቀር ተቀምጦል። ታዲያ እኚን የመሰሉ የእግዚአብሔር ድንቅ ስራ መገለጫ የሆኑ አባት በሁሉ ዘንድ የተመሰግኑ ቢባሉ በትክክል ቢገልጻቸው እንጂ ምንየሚያስተች ነገር አለው ።
አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን ያብዛልን
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር